የአፍሪካ ህብረት ኢትዮጵያና ኤርትራ ግንኙነታቸውን ለማሻሻል የጀመሩትን ስራ አደነቀ

(ኤፍ.ቢ.ሲ)- የአፍሪካ ህብረት ኢትዮጵያና ኤርትራ በመካከላቸው ያለውን ግንኙነት ለማሻሻል የተጀመሩትን በጎ ስራዎች አደነቀ።

የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሳ ፋቂ መሃመት በሰጡት መግለጫ ኢትዮጵያ የአልጀርሱን ስምምነት እና የድንበር ኮሚሽኑን ውሳኔ ሙሉ በሙሉ ለመተግበር መወሰኗን አድንቀዋል።

እንዲሁም የኤርትራው ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ በትናንትናው እለት በሰጡት መግለጫ ኤርትራ ከኢትዮጵያ ጋር ገንቢ ውይይት የሚያደርግ ከፍተኛ ልዑኳን ወደ አዲስ አበባ ልትልክ መሆኑን ማስታወቃቸውን እንዳሚያደንቁም ገልፀዋል።

የህብረቱ ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሳ ፋቂ መሃመት፥ ለኢትዮጵያ እና ኤርትራ እንዲሁም ለሁለቱ ሀገራት መሪዎች ማለትም ለጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ እና የኤርትራው ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

በኢትዮጵያ እና በኤርትራ መካከል የትብብር እና የመልካም ጉርብትና ምእራፍ እንዲከፈት የሚደረገውን ጥረት እንደሚደግፉም ሊቀመንበሩ አስታውቀዋል።

በሁለቱ ሀገራት መካከል የሚኖረው ዘላቂ ስላም ለምስራቅ አፍሪካ ቀጠና እና አጠቃላይ ለመላው የአፍሪካ ሰላም ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንዳለውም ገልፀዋል።

በተጨማሪም ኤትዮጵያ እና ኤርትራ አሁን ላይ ሰላምን ለማስፈን የጀመሩት እንቅስቃሴ እንደ አውሮፓውያኑ በ2020 በአፍሪካ ላይ ያለውን ግጭት እና ጦርነት ለማስቆም የተያዘው እቅድ ግቡን እንዲመታ የሚያግዝ ነውም ብለዋል።

የህብረቱ ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሳ ፋቂ መሃመት አክለውም በሁለቱ ሀገራት መካከል ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን የሚደረገው ጥረት ግቡን እስኪመታ ድረስም የአፍሪካ ህብረት አስፈላጊውን ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ መሆኑን አስታውቀዋል።

የኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ባለፈው ግንቦት ወር መጨረሻ ባካሄደው ስብሰባ የኢትዮ- ኤርትራ ወቅታዊ ሁኔታን በመገምገም፥ ኢትዮጵያ የአልጀርሱን ስምምነትና የድንበር ኮሚሽኑን ውሳኔ ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ ተቀብላ ለመተግበር መስማማቷን መግለጹ ይታወሳል።

ይህን ተከትሎም በኢትዮጵያና ኤርትራ መካከል ተፈጥሮ የቆየው አለመግባባት እንዲያበቃና በሁለቱ ወንድማማች ህዝቦች መካከል ዘላቂ ሰላም እንዲፈጠር ጥሪ ማቅረቡም የሚታወስ ነው።

በዚሁ መሰረት የኤርትራው ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ በትናንትናው እለት፥ ኤርትራ ከኢትዮጵያ ጋር ገንቢ ውይይት የሚያደርግ ከፍተኛ ልዑኳን ወደ አዲስ አበባ እንደምትልክ አስታውቀዋል።

%d bloggers like this: